ሪካርዶ ካላፊዮሪ መድፈኞችን በይፋ ተቀላቀለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጣልያናዊው ተከላካይ ሪካርዶ ካላፊዮሪ በረጅም ጊዜ ኮንትራት ከቦሎኛ አርሰናልን ተቀላቅሏል፡፡
የ22 ዓመቱ ተጫዋች በቦሎኛ የተከላካይ ክፍል ላይ ምርጥ ብቃቱን ካሳየ በኋላ በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ወደ ጀርመን ያመራው የጣልያን ብሄራዊ ቡድን ስብስብ አባል ነበር፡፡
በጣልያኑ ክለብ ሮማ አካዳሚ ውስጥ 12 ዓመታትን ያሳለፈው ካላፊዮሪ በሴሪ ኤው ከታዩ ወጣት የተከላካይ ከዋክብቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን÷ በውድድር ዓመቱ 5ኛ ደረጃን ይዞ ባጠናቀቀው ቦሎኛ ድንቅ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል፡፡
ወጣቱ ተከላካይ በፕሪሚየር ሊጉ ለተከታታይ ዓመታት የዋንጫ ፉክክር እያደረገ የሚገኘውን የሚኬል አርቴታ ቡድን የተከላካይ ክፍል ያጠናክራል ተብሎ ታምኖበታል፡፡