በከተማ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስፋት በትኩረት ይሰራል – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት በከተማ ልማት ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የሐረር ከተማን ስትራቴጂክ ዕቅድ ለመምራት ከተዋቀረው ግብረሀይል ጋር በክልሉ ተጀምረው በሂደት ላይ በሚገኙ እና በበጀት ዓመቱ ተግባራዊ በሚደረጉ አዲስ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ መክረዋል።
የማህረሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ በመሰረተ ልማት፣ በከተማ ውበት እና ፅዳት ስራ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አቶ ኦርዲን ገልፀዋል።
በበጀት ዓመቱ በተለይ በኮሪደር ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ማህበረሰቡን ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚያደርጉና የማህበረሰቡን ይሁንታ ያገኙ ናቸውም ብለዋል፡፡
የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናቀቀ በ2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለማስጀመር ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ነው ያሉት፡፡
አዳዲስ የገበያ ሼዶችን በመገንባት በመንገድ ላይ የሚካሄዱ ስርዓት አልባ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ስርዓት ለማስያዝ እንደሚሰራም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በከተማ ውበት እና ፅዳት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በመግለጽ በመስክ ምልከታ የፕሮጀክቶች አፈፃፀምን ክትትል እና ድጋፍ እደሚደረግም አቶ ኦርዲን ተናግረዋል።
እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍ የመንጃ ፍቃድ፣ ቦሎ እና ታርጋ ቁጥጥርን በማጠናከር በህገ ወጦች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ተቀምጧል ተብሏል፡፡