Fana: At a Speed of Life!

አልኮሆል ያለአግባብ መጠቀምና ሱሰኝነት ያለው ተፅዕኖ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አልኮሆል ያለአግባብ መጠቀም እና ጥገኛ መሆን በህይወትዎ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል።

አልኮሆልን ያለአግባብ መጠቀም ማለት አልኮልን ከመጠን ያለፈ ወይም በብዛት መጠቀም ሲሆን፤ የአልኮሆል ጥገኛነት ለተወሰነ ጊዜ አልኮሆልን ያለማቋረጥ ሲጠቀሙ እና በዚህ ምክንያት ሰውነትዎ ሲለወጥ የሚፈጠር ነው፡፡

የአልኮሆል ጥገኛ ከሆኑ ካልጠጡ ሊታመሙ ወይም የተለየ ስሜት ሊሰማዎት ስለሚችል አልኮሆል መጠጣትን ማቆም ከባድ ይሆንብዎታል።

አዘውትረው አልኮሆል በብዛት የሚጠጡ ሰዎች የአልኮሆል አጠቃቀም መታወክ ተብሎ የሚጠራውን ሊያዳብሩ ይችላሉ።

አልኮሆል ያለግባብ መጠቀም እና ጥገኝነት:-

ከመጠን በላይ መጠጣት ወደ ሱስ ሊያመራ ይችላል፤ በመደበኛነት ለመስራት አልኮሆል እንደሚያስፈልጎ ሊሰማዎት ይችላል፤ ጠዋት ላይ ከስራዎ በፊት፣ በቀን ወይም ምሽት ከስራ ወደ ቤት እንደገቡ አልኮሆል እንዲጠጡ የሚያስገድድ ስሜት ሊሰማዎት ይችላል።

የአልኮሆል አሉታዊ ተጽዕኖ:-

ደካማ የስራ አፈጻጸም፣ ሥራ ማጣት፣ የገንዘብ ችግሮች፣ የመኪና አደጋ ተጋላጭነት፣ ከጓደኞች እና ቤተሰብ ጋር ያለ ግንኙነት ላይ ችግሮች መከሰት፣ ስራ ባልደረቦች፣ ጓደኞች እና ቤተሰብ አመኔታ እና ክብር ማጣት ይጠቀሳል።

እንዲሁም ለረጅም ጊዜ መጠጣት ሰውነትዎን እና አዕምሮዎን በዘለቄታዊነት ይጎዳል፤ እንዲሁም የዕድሜ ልክ የጤና ችግሮችን ያስከትላል እነዚህም በጉበትዎ ወይም በቆሽትዎ ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ የልብ ችግር፣ የደም ግፊት ወይም የስትሮክ ችግር፣ የካንሰር ህመም፣ ኢንፌክሽኖችን የመከላከል አቅም መቀነስ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የአንጎል ወይም የነርቭ ጉዳት፣ የመንፈስ ጭንቀትና ያለጊዜ ሞት ያስከትላል፡፡

አልኮሆልን ያለግባብ መጠቀም መንስኤዎች:-

የአልኮሆል መጠጥ ያለአግባብ የመጠቀም የቤተሰብ ታሪክ ያለው፤ የመንፈስ ጭንቀት ወይም ሌሎች የአዕምሮ ጤና ሁኔታዎች መኖር፣ ገና በልጅነት መጠጣት መጀመር፣ ብዙ ጊዜ ከመጠን በላይ መጠጣት፣ በልጅነት ጊዜ የስሜት ቀውስ፣ ጭንቀት እና ያልተረጋጋ የቤተሰብ ህይወት ማጋጠምና ብዙ ጊዜ ከሚጠጡ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ናቸው።

የአልኮሆል ጥገኝነት ችግር እንዳለብዎ ካሰቡ መጠጣት ለማቆም መወሰን፡-

አልኮሆልን በተደጋጋሚ መጠጣት ከተለማመዱ ይህን ማድረግ በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡

መጠጣትን የመተው ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ከጤና እንክብካቤ አቅራቢዎ ወይም ከምያምኑት ሰው ጋር መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ከዘውዲቱ ሆስቲታል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

እነዚህ ምልክቶች ጭንቀት፣ መንቀጥቀጥ፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ላብ ወይም መተኛት አለመቻልን ሊያካትቱ ይችላሉ።

አልኮሆል ያለአግባብ መጠቀም ለማቆም በማህበራዊ ስብሰባዎች እና አልኮሆል ባለባቸው ቦታዎች አልኮሆል ያልሆኑ መጠጦችን ለመጠጣት ይምረጡ፤ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባሉ አልኮሆልን በማያካትቱ በሚወዷቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ብዙ ጊዜ ያሳልፉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.