በውጭና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሚሳተፉበት ለአንድ ሳምንት በሚቆየው 3ኛው ዓመታዊ የድሬ ናፍቆት በዓል ከትናንት ምሽት ጀምሮ እየተካሄደ ነው።
በበዓሉ ላይ በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እና በሀገር ውስጥ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ተሳታፊ ሆነዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይም ከንቲባ ከድር ጁሃር÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከበረው የድሬ ናፍቆት በዓል የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የእርስ በርስ ግንኙነትና ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ያጠናከሩበት ነው ብለዋል።
በተለይ በመላው ዓለም የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በድሬዳዋ ማህበራዊ ልማቶች ላይ በመሳተፍ መሠረታዊ ችግሮችን በማቃለል ረገድ የጎላ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
እንዲሁም በተመቻቸላቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ በማምረቻ፣ በጤና፣ በሆቴል፣ በንግድና ሌሎች ዘርፎች ላይ ተሰማርተው በሺህ ለሚቆጠሩ ወገኖች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አመልክተዋል።
በተጨማሪም በበጎ ፈቃድ ስራዎች እና በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻዎች ላይ በመሳተፍ የድርሻቸውን እንደተወጡ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመድረኩ አቶ ከድር ጁሃር የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በድሬዳዋ አሸዋ የገበያ ማዕከል እና በጎፋ ዞን በደረሰው አደጋ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍና በማቋቋም የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።