Fana: At a Speed of Life!

እስከ አሁን የ232 ወገኖች ሕይወት አልፏል- ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ እስከ አሁን የ232 ወገኖች ሕይወት ማለፉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ አረጋገጡ፡፡

እንዲሁም 10 ሰዎች በተደረገላቸው ሕክምና መትረፋቸውን እና ከ500 በላይ ወገኖች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ ርዕሰ መሥተዳድሩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

እስከ አሁንም ከ70 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መደረጉን ገልጸው÷ ከዚህ ውስጥ በገንዘብ 16 ሚሊየን መሆኑን እና ቀሪው ደግሞ በዓይነት ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

አደጋውን ተከትሎ በማጽናናትና ድጋፍ በማድረግ ከተጎጅወች ጎን ለቆሙ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ተላልፎ እንደነበር በማስታወስ እና 88 አባዎራዎች ከአካባቢው እንዲወጡ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ የመሬት መንሸራተት አደጋው መከሰቱንም አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ለመሰል አደጋ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ እየሠራም እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

በታሪኩ ለገሰ፣ ማቱሳላ ማቴዎስ እና መለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.