Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለብልጽግናና ብዝኃነት አደረጃጀት አባላት አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለብልጽግናና ብዝኃነት አደረጃጀት አባላት አዲስ አበባ ገቡ።

ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የመከላከያና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ተወካዮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባቸውም የአደረጃጀቱ ፕሬዚዳንት ጋሻው በርቦ አስገንዝበዋል፡፡

አደረጃጀቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በገንዘብ ከመደገፍ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የተነደፉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በማድረግ ያለንን አጋርነት ለማሳየት ኢትዮጵያ መጥተናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ሠራዊቱ እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የበለጠ በማቀፍና በማሳተፍ የሚያበረክቱትን አስተዋጽዖ የበለጠ ለማሳደግ እንደሚረባረቡ ጠቁመዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ አባላትም÷ ለውጡን ማስቀጠልና መከላከያን ለመደገፍ በማለም ወደ ኢትዮጵያ መጥተናል ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ኮሎኔል ሲራጅ ሲንቢሩ በበኩላቸው÷ የዳያስፖራ አባላቱ ሠራዊቱ እየከፈለ ላለው ዋጋ እውቅና መስጠቱ የሚመሰገን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሌሎች የዳያስፖራ አባላትም ይህን አርዓያ በመውሰድ ከሠራዊቱ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አባላቱ ለመከላከያ ሠራዊት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር በተለያዩ በጎ ተግባራት እንደሚሳተፉ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወንድወሰን ግርማ ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.