አምባሳደር ሙክታር (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ ለነበራቸው ስኬታማ ጊዜ የስንብት ሽኝት ተደረገላቸው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡበ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ዲፓርትመንት ሚኒስትር ዶናልድ ላሞላ በሀገራቸው የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ላገለገሉት ሙክታር ከድር (ዶ/ር) የክብር ስንብት ሽኝት አደረጉላቸው፡፡
በደቡብ አፍሪካ የነበራቸውን የሥራ ጊዜ ያጠናቀቁት አምባሳደር ሙክታር (ዶ/ር)÷ በቆይታቸው የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል በማድረግ የሀገራቱን ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም 4ኛው የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስበስባ በአዲስ አበባ መካሄዱና በርካታ የትብብር ማጠናከሪያ ስምምነቶች መፈረማቸው፣ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ ያሸጋገረ ስምምነት መፈረሙ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ግጭት ያስቆመው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መፈረሙን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና የደቡብ አፍሪካን የሁለትዮሽ ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠው÷ አምባሳደሩ በቆይታቸው የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ትብብሮች ለማሳዳግ መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡