Fana: At a Speed of Life!

ከሐምሌ 23 ጀምሮ በሰበታና ዶዶላ ለ20 ሺህ ወገኖች ነጻ የዓይን ሕክምና ይሰጣል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አል ባሳር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ከሐምሌ 23 እስከ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በሰበታና ዶዶላ ጤና ጣቢያዎች ለ20 ሺህ ሰዎች ነፃ የዓይን ሕክምና እንደሚሰጥ ተገለፀ።

የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር ያሲን ራጆ፣ የሸገር ከተማ ጤና ጽ/ቤት የጤና ማበልፀጊያና የበሽታ መከላከል ዳይሬክተር አበበ ዘውዴ እና የጽ/ቤቱ ተወካይ ጌታሁን ፖሊሲ እንዲሁም የሰበታ ክፍለ ከተማ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ ሳሙኤል ይልማ ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በሰበታ ጤና ጣቢያ ከሐምሌ 23 እስከ ሐምሌ 25 እና በዶዶላ ኑቬሬን ጤና ጣቢያ ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ለ20 ሺህ ወገኖች ነጻ የዓይን ሕክምና እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ያስታወቁት ኃላፊዎቹ ÷ ሕብረተሰቡ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፋውንዴሽኑ ከፈረንጆቹ  2000 እስከ 2024 በኢትዮጵያ ከ700 ሺህ ለሚልቁ ወገኖች የዓይን ምርመራ  እና ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደግሞ የዓይን ቀዶ ጥገና ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.