Fana: At a Speed of Life!

ልማት ባንክ የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ አልሚዎችን እንደሚደግፍ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ልማት ባንክ በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሚሰማሩ አልሚዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡

በፓርኩ ውስጥ እያለሙ ከሚገኙ እና ከአዳዲስ ባለሀብቶች ጋር የኢንቨስትመንት ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሰሩ አልሚዎች የብድር አገልግሎት በተቀላጠፈ መልኩ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የውጭ ምንዛሬ፣ የመሠረተ ልማት፣ ቢሮክራሲ የበዛበት አሰራር እና ሌሎች ተግዳሮቶች ሊቀረፉ እንደሚገባም አንስተዋል።

በመድረኩ የተገኙት የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሃንስ አያሌው (ዶ/ር)፥ ልማት ባንክ በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን እገዛና ትብብር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ አልሚዎች ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

በብድር አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሊስተዋሉ የሚችሉ የአሠራር ቢሮክራሲዎችን ለመቅረፍ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከባለሃብቶቹ ለተነሱት ጥያቄውች በሰጡት ማብራሪያ፥ በሲዳማ ክልል የሚያለሙ ባለሃብቶች የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ኮሚቴ ይቋቋማል ብለዋል።

ችግሮችን ለመፍታት እና ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተፈጻሚነት ተገቢ ክትትል እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሙሉነህ ለማ በበኩላቸው፥ በሲዳማ ክልል በአምራች ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የብሔራዊ ባንክን መመሪያ በመከተል የብድር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነን ብለዋል።

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አሰፈጻሚ አቶ ሃይሉ የተራ፥ በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ አስፈላጊው መሠረተ ልማት በመሟላቱ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.