Fana: At a Speed of Life!

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አፍሪካዊ ተቋም ሆኖ ከፍተኛ የመማር ማስተማር ሥራ እየሠራ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊ ተቋም ሆኖ ከፍተኛ የመማር ማስተማር ሥራ እየሠራ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

ስትራቴጂክ የደህነት ጉዳዮችን መረዳት፣ መተንተንና አማራጮችን ማመንጨት የሚችሉ የደህንነትና ስትራቴጂክ ዘርፍ መሪዎችን የማፍራት ተልዕኮ ተቀብሎ እየሰራ የሚገኘው የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በአጭርና በረጅም ኮርስ በመደበኛና በማስተርስ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አፍሪካዊ ተቋም ሆኖ በደኅንነት ላይ ያተኮረ ስራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋሙ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆንም የማጠናከር ሥራ እንሰራለን ብለዋል።

ተመራቂዎችም ያገኙትን አቅም ከቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር በማዋቀር የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ የኢትዮጵያን ደህንነትና ሠላም ለማስጠበቅ ከሚሰሩ ተቋማት አንዱ መሆኑን የገለጹት የኮሌጁ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ቡልቲ ታደሠ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች በደህንነትና ስትራቴጂክ ዘርፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በባህልና ዲፕሎማሲም የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ኮሌጁ በመደበኛ እና በማስተርስ ፕሮግራም ያስተማራቸው ተማሪዎች ከመከላከያ፣ ከፌዴራል ተቋማት እና ከስድስት የአፍሪካ ሀገራት መካተታቸውን አዛዡ ተናግረዋል።

ተመራቂዎችም በትምህርት ቆይታቸው የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነትን ከማስጠበቅና ወታደራዊ ዲፕሎማሲያዊ ሂደቶችን ከማጠናከር አንፃር ጥሩ ዕውቀት ማግኘታቸውን ገልፀው፤ የሚሰጡ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ግዳጆችን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.