ጉምሩክ ኮሚሽን 191 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በ2016 በጀት ዓመት 191 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለፀ።
ኮሚሽኑ የዓመታዊ አፈፃፀም ግምገማውን ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ከመጡ አመራሮች ጋር በመሆን በአርባ ምንጭ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።
በግምገማው መክፈቻ ወቅት ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ÷ የእዳ አሰባሰብ ስርዓት፣ የወጪ እና ገቢ ንግድ እንዲሁም የኮንትሮባንድ ስራዎች በመሻሻላቸው በ2016 በጀት አመት ስኬት ሊመዘገብ ችሏል ሲሉ ገልፀዋል።
በጠቅላላው 191 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸው፥ ይህም የእቅዱን 90 በመቶ ይሸፍናል ብለዋል።
ይሁንና የእዳ አሰባሰብ ላይ በበቂ ሁኔታ ባለመሰራቱ ሲንከባለል የመጣ 17ቢሊየን ብር መኖሩን ገልጸው፥ በገቢና በወጪ ንግድ በህጋዊ ሽፋን የሚፈጠር የንግድ ማጭበርበር ፈተና ሆኖ በዓመቱ መቀጠሉን ጨምረው ገልፀዋል።
የግምገማ መድረኩ በየዘርፉ የሚቀጥል ሲሆን ፥ በቀጣይ ቀናት ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመሆን የእቅድ ውይይት እንደሚኖር ይጠበቃል።
በዳዊት ጎሳዬ