ጀኔራል መኮንኑ ዕዙ ከክፍለ ጦር አመራሮች እና ከመምሪያ ኃላፊዎች ጋር ለሁለት ቀን ባደረገው ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው እንዳሉት፤ አሁን ባለው እውነታ ፅንፈኛው ኃይል ተመቷል።
የቀረውም ቢሆን በሰፈር እና በጎጥ የተከፋፍሎ በስልጣን ፍላጎትና በሰበሰበው ገንዘብ እየተጣላ እንዲሁም እርስ በእርሱ እየተገዳደለና አንዱ በአንዱ ላይ እየዘመተ ተራ ሽፍታ ሆኗል ነው ያሉት።
በውሸት ፕሮፖጋንዳ የአማራ ህዝብ ጥያቄ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የተለየ አስመስሎ ሲሰብከው የነበረው ማህበረሰብም የፅንፈኛውን ሴራ አውቆ ቡድኑን መደገፍም ሆነ መርዳት እንደማያስፈልግ መግባባት ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ከአሁን በፊት በነበሩት በርካታ ግዳጆችም ወደር የሌላቸው አኩሪ ገድሎችን የፈፀመ ጀግና ክፍል መሆኑን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ሰዓት አቅሙን አጎልብቶ በበቂ ደረጃ የተደራጀ በመሆኑ በቀጣይም ብዙ የሚጠበቅበት የማይበገር የህዝብና የሀገር ትልቅ አለኝታ ስለሆነ የቀጣይ ተልዕኮውንም በውጤት ይፈፅማል ብለዋል ጄኔራል አበባው ታደሰ።
የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ በበኩላቸዉ የክፍሉ የሠራዊት አባላት ከላይ እስከታች እጅና ጓንት ሆነው ለሀገራቸው ሰላምና ደህንነት በመሥራታቸው በዓመቱ ድል ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ሀገሩን እና ህዝቡን እያሰበ የሚሰራ ሠራዊት ሁሌም አሸናፊ ነው ሲሉም መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ የተነሳም በሰንደቅ ዓላማዋ ስር በገባነው ቃል መሠረት ለህዝባችን ለሀገራችን በትጋት በፍፁም ጀግንነት በመስራት ሰላሙን በዘላቂነት በማረጋገጥ ልማትና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ያለ እንቅፋት እንዲቀጥል ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።