Fana: At a Speed of Life!

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በተለያዩ መስኮች መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በተለያዩ መስኮች መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የተዘጋጀውን ዐውደ ጥናት ተካፍለናል ብለዋል፡፡

ዐውደጥናቱ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች የተገኙበት እና በቢግ ዳታ፣ ጄኔሬቲቭ ኤ.አይ፣ በአመራሮች ውሳኔ አሰጣጥ፣ በፖሊሲ እና ሕዝብን በማገልገል ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ውጤታማነትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ግንዛቤ የተወሰደበት እንደሆነ ገልጸዋል።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአሁኑ ወቅት በሁሉም መስኮች አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ በመንግሥት አሰራሮች፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና በሌሎችም መስኮች መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

እኛም በዚህ ዘርፍ በርትተን በመስራት እና የሕዝባችንን ችግሮች መፍታት የሚችሉ የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን በማበልፀግ መጠቀም ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂውን ሙሉ አቅም ተገንዝቦ ወደተግባር የሚለውጥ የሰው ኃይል መገንባት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አንጻር እንደነዚህ ያሉ ዐውደ ጥናቶች ጉልህ ሚና እንዳለቸው እናምናለን ብለዋል፡፡

በወዳጅ ሀገር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተቀማጭነቱን ባደረገው ፕሪሳይት በተባለው ተቋም ለሦስት ቀናት የተዘጋጀው ዐውደ ጥናት በዘርፉ ያቀድነውን ወደመሬት ለማውረድ ከሚሰጠው አቅጣጫ አንጻር ስኬታማ ነበር ሲሉ አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.