የመድሃኒት ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚካሄደውን ቁጥጥር ህብረተሰቡ እንዲያግዝ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመድሃኒት ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚካሄደውን ቁጥጥር ህብረተሰቡ እንዲያግዝ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ጥሪ አቀረበ።
ባለስልጣኑ የመድሃኒት ደህንነት ቁጥጥርን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ እንደሆነ አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ የመድኃኒት ደኅንነት ክትትልና የሕክምና ሙከራ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አስናቀች ዓለሙ እንደገለፁት፤ የመድሃኒት ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ቁጥጥር የጤና ባለሙያዎችና ተጠቃሚው ህብረተሰብ ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው።
በመሆኑም በጤና ተቋማት ባለሙያዎች ከሚያደርጉት የመድሃኒት ደህንነት ክትትል ባሻገር ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት እንዲወጣ ጠይቀዋል።
መድሃኒት ተጠቃሚ የሆነ ማንኛውም ሰው መድሃኒት በሚታዘዝለት ወቅት ስለ መድሃኒቱ አስፈላጊውን መረጃ ከባለሙያ ጠይቆ መረዳት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
መድሃኒቱን በሚጠቀምበት ወቅትም የጎንዮሽ ክስተት ካጋጠመው መድሃኒቱን ወዳዘዘለት ባለሙያ በመሄድ ማሳወቅና የሚሰጠውን ምክር እና ህክምና በአግባቡ መተግበር አለበት ማለታቸውን የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል።
የጤና ባለሙያውም የመድኃኒት አወሳሰድ ስርዓትና ስለሚያጋጥሙ የጎንዮሽ ክስተቶች ለታካሚዎች ቀድሞ የማሳወቅ እና ችግር ካጋጠመም አስፈላጊውን ህክምና የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።