Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሶማሊያ መንግስት የሚሰጡ የትንኮሳ መግለጫዎችን በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሊያ መንግስት በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን የትንኮሳ መግለጫዎች ኢትዮጵያ በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ÷ የሶማሊያ መንግስት ከሚያቀርባቸው መሰረተ ቢስ ክሶች በተቃራኒ ኢትዮጵያ ወንድም ለሆነው የሶማሊያ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ከሦስት አሥርት ዓመታት ለበለጠ ጊዜ መስዋዕትነት እየከፈለች እንደምትገኝ አመላክቷል፡፡

ይሁንና ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መልሶ ግንባታ የከፈለችውን ዋጋ በዘነጉ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት እየተሰነዘረባት ባለው በርካታ ሃላፊነት የጎደለው ክስ ማዘኗን መግለጫው አንስቷል፡፡

በመሆኑም ለቀጣናዊ ነፃነት፣ ባህላዊ ትስስር፣ በደምና በላብ የተገነባውን ታሪካዊ ግንኙነት ከግምት በማስገባትም ኢትዮጵያ ለተሰነዘሩባት መሠረተቢስ ክሶች ምላሽ መስጠትን እንዳልመረጠች አመልክቷል፡፡

ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያ ለሀገራቱ ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ትዕግስትንና አዎንታዊ ተሳትፎን አማራጭ ማድረጓን ነው መግለጫው ያመላከተው፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሚደረጉ ህገወጥ የቀላል ጦር መሳሪያዎች ዝውውር ጉዳይ በጥልቀት እንደሚያሳስባት ሊሰመርበት እንደሚገባም መግለጫው አስገንዝቧል፡፡

ቀጣናው በግጭቶች፣ በማይፈተሹ የጠረፍ መስመሮች እንዲሁም በድንበር የደህንነት ችግሮች እየታመሰ በመሆኑ የቀጣናው ሀገራት እንዲህ ዓይነት ወንጀሎችን ለመዋጋት ኃይላቸውን ለማሰባሰብ እንደሚያገደዱ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን፣ አነስተኛና ቀላል የጦር መሳሪያ ዝውውርን እና የፈጠራ ፈንጂዎችን የመከላከልና የመዋጋት የፀና አቋም እንዳላትም መግለጫው አስምሮበታል፡፡

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከወንድም የሶማሊያ ህዝብ ጋር ከሰላም፣ ከመረጋጋት፣ ከምጣኔ ሀብታዊ እድገት እና ቀጣናዊ ትብብርን ከማስቀጠሉ ጎን እንደምትቆም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.