በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የኢንቨስትመንት እድሎችና አማራጮች ላይ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፉ የንግድና ፋይናንስ ተቋም ቡድን ጋር በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የኢንቨስትመንት እድሎች እና አማራጮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡
ሚኒስትሩ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ባለሀብቶችን ያካተተው ቡድን ጋር የመከሩ ሲሆን÷ በውይይቱ በኢትዮጵያ የደረቅ ወደቦች መሠረተ ልማትና በሎጂስቲክስ ማዕከል ልማት ላይ መምከራቸው ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በባቡር መሠረተ ልማት፣ በትራንስፖርት መሠረተ ልማትና አገልግሎት እንዲሁም በአቪዬሽን ዘርፍ ባሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እና አማራጮች ዙሪያ ውይይት ማሄዱን አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ባለሀብቶቹ ኢትዮጵያ ባላት ዕምቅ ሀብት፣ ምቹ የቢዝነስ ከባቢ እና አዋጭ ገበያ በመሳብ በተለያዩ የዘርፉ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውም አረጋግጠዋል ተብሏል፡፡