Fana: At a Speed of Life!

የመልካ ቁንጡሬ ባልጪት የአርኪዮሎጂና ፓሊዮንቶሎጂ ሥፍራ በዩኔስኮ ተመዘገበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመልካ ቁንጡሬ ባልጪት የአርኪዮሎጂ እና ፓሊዮንቶሎጂ ሥፍራ በዓለም ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግቧል፡፡

በሕንድ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው 46ኛው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ማዕከል ዓመታዊ ጉባዔ የመልካ ቁንጡሬ ባልጪት የአርኪዮሎጂ እና ፓሊዮንቶሎጂ ሥፍራ ሶስት መስፈርቶችን በማሟላት የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ተገልጿል፡፡

ሥፍራውን ለዓለም ቅርስነት ካበቁት መስፈርቶች መካከል ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዓመት እስከ መጨረሻው የድንጋይ ዘመን የሰው ልጅ ይጠቀምባቸው የነበሩ የድንጋይ መገልገያዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዓመት እድሜ ያላቸው የተለያዩ የሰውና የእንስሳት ቅሪተ አካሎች በብዛት የሚገኙበት ስፍራ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም የሰው ልጅ ከድንጋይ የተለያዩ መገልገያዎችን ይሰራ እንደነበር የሚያሳዩ ስምንት የባልጩትና ሌሎች የድንጋይ መሳሪያ ማምረቻ ሥፍራዎችን ይዞ የሚገኝ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ለጉባኤው በላኩት የፅሁፍ መልእክት÷ ቅርሱ የተመዘገበው ሉሲ የተገኘችበትን 50ኛ አመት በሚከበርበት ወቅት መሆኑ ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ቅርሱ ተጠብቆ እንዲቆይም የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግም ማረጋገጣቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

መልካ ቁንጡሬ ባልጪት ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ በሚወስደው መንገድ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አዋሽ ወንዝ ዳርቻ ላይ የሚገኝ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው ቋሚ የሚዳሰሱ ቅርሶች 12ኛው ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.