Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አካታችና አሳታፊ ባደረገ መልኩ እንዲከናወን ጥረት እየተደረገ ነው – ፕ/ር መስፍን አርአያ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል አካታችና አሳታፊ ባደረገ መልኩ እንዲከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናገሩ።

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክሩ ያላቸውን ተሳትፎና ሚና ለማጠናከር ያለመ ውይይት በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።

በዚሁ ወቅት መስፍን አርአያ (ፕ/ር)÷ ሀገራዊ ምክክሩን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል ባካተተ መልኩ ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚሁ ሲባል ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር መድረኩን ማዘጋጀቱን አንስተዋል።

ዜጎችን ለአካል ጉዳተኝነት ከሚዳርጉ ችግሮች መካከል የሰላም መደፍረስና የጦርነት መደጋገም አንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ ሃገራዊ ሰላም ማስፈኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው÷ አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ የማንቃት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክር በሚያመጣው ዘላቂ መፍትሔ ውስጥ አካል ጉዳተኞች የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የለውጥ ሀሳብ በማምጣት ረገድ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.