Fana: At a Speed of Life!

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ መሰረት ተጎጂዎችን የመደገፍ ስራ እየተከናወነ ነው – አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከሰብዓዊ ድጋፍ ጀምሮ የመልሶ ማቋቋም ስራው በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)÷ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተከሰተው አደጋ የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ያሉበት ቡድን በአካባቢው ተገኝቶ ማህበረሰቡን የማፅናናት፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶችና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን የመለየት ስራ አከናውነዋልም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአደጋው በተከሰተበት ዙሪያ እንዲነሱ የተደረጉትን 600 ሰዎችን ጨምሮ በቀጣይ መነሳት ያለባቸው ተጨማሪ 6 ሺህ የሚጠጉ ተጋላጮች የተለዩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት ጎን ለጎን የመልሶ ማቋቋም ስራዎች በተደራጀና በባለሙያ ጥናት በሚለይ ቦታ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከአጭር ጊዜ አኳያ ለሚከናወኑ የህይወት አድንና መልሶ የማቋቋም ስራዎች ፈፃሚ አካላት እንደተለዩ ጠቅሰው÷ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ የማስተባበርና የማቀናጀት አደረጃጀትም ተፈጠሯል ነው ያሉት፡፡

ኮሚሽኑ አደጋው ከተከሰተበት እለት ጀምሮ ጥልቅ ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ በሚያሳይ መንገድ ለተደረገው ሰብዓዊ ድጋፍና ትብብር ሁሉንም አካላት አመስግኗል፡፡

በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.