Fana: At a Speed of Life!

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ጉባዔ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የነበረው 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን በማፅደቅ አጠናቅቋል፡፡

ምክር ቤቱ ካፀደቃቸው ረቂቅ አዋጆች መካከል የከተማ ቆሻሻ አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ፣ የፋይናንስ ረቂቅ አዋጅ፣ የግዥና ንብረት አስተዳድር ረቂቅ አዋጅ፣ የዋና ኦዲተር ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ ይጠቀሳሉ።

የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ እና የግብርና ስራ ገቢ ግብር ረቂቅ፣ የክልሉን የአመራር አካዳሚ ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ እና የምግብና መድሀኒት ጤና እና ጤና ነክ ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ፣ የደን ልማትና ጥበቃ አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ፣ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ እና የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለማቋቋም የወጣ ረቂቁ አዋጆችም ይገኙበታል።

በጉባዔው በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቅራቢነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የማረቆ ብሔረሰብን ወክለው የተመረጡት ጀማል ማሮ የተመረጡበትን ህዝብ ወክለው በፌደሬሽን ምክር ቤት አባል እንዲሆኑ የቀረቡ ሲሆን ፥ ምክር ቤቱም ሹመቱን አፅድቋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያገለግሉ 94 ዕጩ ዳኞችን ሹመትን ማጽደቁም ነው የተገለጸው።

ከነዚህም መካከል 13ቱ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ሲሆኑ ፥ ቀሪዎቹ ለዞን፣ ለከተማ አስተዳደርና ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የሚያገለግሉ ዳኞች ናቸው።

በመሆኑም የዳኞቹ ሹመት በአንድ ተቃውሞ፣ በሁለት ድምፀ- ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ መጽደቁን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.