Fana: At a Speed of Life!

በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሀገራቸውን የሚያስጠሩ ባለተሰጥኦ ወጣቶች እየተፈጠሩ ነው- ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ሀገራቸውን የሚያስጠሩ በርካታ ባለተሰጥኦ ወጣቶች እየተፈጠሩ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡

ኢንስቲትዩቱ የታዳጊ ወጣቶችን የቴክኖሎጂና ፈጠራ አቅም ለማሳደግ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን የክረምት ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር ኢ/ር) እንደገለጹት÷ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ በትኩረት መስራት ለሀገር እድገት መሰረት ነው።

ኢንስቲትዩቱ ለዘርፉ እድገት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ባሻገር አዳዲስ እውቀት የሚያገኙበት የተደራጀ የክረምት ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያውና 2ኛው ዙር ሥልጠና ተሰጥኦዋቸውን ወደ ውጤት በመቀየር ከግል ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት የሚችሉበት እድል መፈጠሩን አስታውሰዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት የክረምት የታዳጊዎች ሥልጠና ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ዓለምን የሚያስጠሩ ባለተሰጥኦ ወጣቶች ባለቤት መሆኗን አሳይቶናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወጣቶች የላቀ እውቀትና ሀሳብ እንዳላቸው ገልጸው÷ አቅማቸውን አውጥተው መጠቀም የሚችሉበትን እድል ማመቻቸት ደግሞ የእኛ ድርሻ ነው ብለዋል፡፡

ለሥልጠናው በዘርፉ የካበተ ልመድ ያላቸው መምህራን፣ ምቹ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች፣ ቤተ ሙከራዎች እና መሰል ግብዓቶች የተሟሉለት ማዕከል መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.