Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሩቶ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ለካቢኔነት አጩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በራይላ ኦዲንጋ ከሚመራው ዋና ተፎካካሪ ፓርቲ አራት ሰዎችን ለካቢኔነት ማጨታቸው ተሰምቷል።

በዚህም ሀሰን ጆሆ የማዕድን፣ የብሉ ኢኮኖሚ እና የባህር ጉዳዮች የካቢኔ ፀሐፊ ሆነው ሲመረጡ፣ ዊክሊፍ ኦፓራኒያ የሕብረት ሥራ ማህበራት የካቢኔ ፀሐፊ፣ ጆን ምባዲ በብሔራዊ ግምጃ ቤት ሚኒስቴር እና ኦፒዮ ዋንዳዪ በኢነርጂ ሚኒስትርነት አቅርበዋል።

አራቱ ፖለቲከኞች የአስር እጩዎች ስብስብ አካል የነበሩ ሲሆን፥ የኦሬንጅ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መሪ የቅርብ አጋር እንደሆኑም ይነሳል።

የኬንያ ፕሬዚዳንት ባለፈው ሣምንት ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ሹመት ሥድስት የቀድሞ የካቢኔ ሚኒስትሮችን አቆይተዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ ተቃዋሚዎች፥ ሚስጥራዊ ስምምነት ተፈጽሟል በማለትም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል ነው የተባለው፡፡

አዚሞ ቴሌቪዥን በትዊተር ገጹ እንዳስነበበው የኦሬንጅ ዴሞክራሲያው ንቅናቄ መሪ ራይላ ኦዲንጋ በፕሬዚዳንቱ የቀረቡ ሹመቶችን ወዳጆቻቸው እንዳይቀበሉ አሳስበዋል ብሏል፡፡

በሀገሪቱ ለሣምንታት የዘለቀው ትርምስ ብዙዎችን ለህልፈት የዳረገ ሲሆን፥ አብዛኞቹን የካቢኔ አባላትን ከኃላፊነታቸው ያስነሳ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ተቃዋሚዎችንም አበርክቷል ነው የተባለው፡፡

በሀገሪቱ ተቃውሞው የጀመረው፥ ኬኒያውያን ተጨማሪ ግብር የሚጥለውን ረቂቅ ህግ ውድቅ ለማድረግ ተቃውሟቸውን ማሰማት በመጀመራቸው እንደሆነ የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.