የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን በጋምቤላ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው በሚኖረው ቆይታ የክልሉን የ2016 በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የስራ ክንውን ሪፖርት አድምጦ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።
የ2017 በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ፣ የማስፈፀሚያ በጀትና ሌሎች ጉዳዮች ላይም ውይይት በማድረግ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተገልጿል፡፡
በጉባዔው ላይ የምክር ቤቱ አባላትን ጨምሮ ከ350 በላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሳተፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ባንቻየሁ ድንገታ÷ የምክር ቤት አባላት የዜጎችን የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።