Fana: At a Speed of Life!

ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን 550 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ማድረጉን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን 550 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ በማድረግ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን እያሟላ መሆኑን ገለጸ።

የልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞቱማ ተመስገን እንደገለጹት፤ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ 550 ሄክታር መሬት ለባለሀብቶች ዝግጁ ተደርጎ መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

ከመሰረተ ልማቶቹ መካከል በኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ 5 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱን ገልጸው፤ በቂ ውኃ ማቅረብ የሚችል መስመር መስከረም ላይ ስራ የሚጀምር መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 230 ሜጋ ዋት ኃይል ማቅረብ የሚችል ንዑስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በቀጣይ ዓመት ጥር ወር ላይ ስራ እንደሚጀምርም አረጋግጠዋል።

በተለይም የወጪ ንግድ ምርቶችን የሚያስፋፉ እና የገቢ ምርቶችን የሚተኩ ኢንቨስትመንቶችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑን ለማስተዋወቅ በተሰራው ስራ 100 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ የተለያዩ ባለሃብቶች ገብተው ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸው፤ ወደ ልዩ ዞኑ በመግባት ሥራ የጀመሩ እንዳሉ ጠቁመዋል።

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ለስራ እድል ፈጠራ፣ትልቅ የኢንቨስትመንት ካፒታልን ለመሳብ፣ የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

ዞኑ ብዙ የኢንቨስትመንት ካፒታልን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት የምንችልበት፣ የወጪ ንግድ ምርቶችን የምናበረታታበት፣ ብዙ ገቢ የምናገኝበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የፌደራል መንግስት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ማጠናከር የሚያስችሉ አዋጆችና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ማውጣቱ ለስራቸው እጅግ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም አውስተዋል።

ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በሞጆና በአዳማ ከተሞች መካከል በ24 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ እየተገነባ ይገኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.