ስድስት ዓመታት ብቻ በቀሩት የመንግስታቱ ድርጅት 17 የልማት ግቦች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገባውን ቃል ለመፈጸም ወደኋላ መቅረቱ ተመላክቷል፡፡
ዓለም በቀውስ ውስጥ እንዳለች ያመላከተው የ2024 የዘላቂ ልማት ግቦች ሪፖርት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያሳደረው ተፅእኖ፣ ግጭቶች እየተባባሱ መሄዳቸው እና የአየር ንብረት መዛባት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር ግስጋሴውን በእጅጉ ገድቦታል ብሏል።
በመሆኑም የ2030 የልማት ግቦችን ለማሳካት ሦስት መሰረታዊ ነገሮችን አስቀምጧል፡፡
ከእነዚህም በቀዳሚነት ተስፋ ባለመቁረጥ በ 2030 አጀንዳ ድህነትን ለማጥፋት፣ ምድርን ለመጠበቅ እና ማንንም ላለመተው የተገባውን ቃል መፈፀም እንደሚገባ አንስቷል፡፡
ለዚህም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ግልጽ ናቸው ያለው ሪፖርቱ÷ ሰላም፣ ደህንነት እና ግጭቶችን በውይይት እና በዲፕሎማሲ መፍታት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።
በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ የብድር መጠን እና የ4 ትሪሊየን ዶላር ዓመታዊ የዘላቂ ልማት ግብ ሙዋዕለ ንዋይ ክፍተት እንደተደቀነባቸው ተነስቷል።
በመሆኑም በዘላቂ ልማት ግቦች ጉባኤ ላይ የዓለም መሪዎች ቃል የገቡትን የ500 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ ማበረታቻ ማሳደግ የዕቅዱን ስኬት ለማፋጠን ወሳኝ መሆኑን አመላክቷል።
ሌላው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከተባበረ ከፍተኛ የስኬት መሻሻሎችን ማምጣት እንደሚችል ነው የተመላከተው፡፡
በዓለም አቀፍ ትብብር አስደናቂ እመርታዎች መታየታቸውን ያነሳው ሪፖርቱ÷ ከ2015 እስከ 2023 የኢንተርኔት አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ 70 በመቶ ከፍ ማለቱን በምሳሌነት ጠቅሷል።
የኤች አይ ቪ ሕክምና ተደራሽነት መጨመር ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ ወደ 21 ሚሊየን የሚጠጉ ከኤድስ ጋር የተዛመዱ ሞትን ማስቀረት መቻሉንም እንደዚሁ አንስቷል።
የልጃገረዶች ከወንዶች ልጆች እኩል በሁሉም ደረጃ ተወዳደሪ መሆን፣ ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን ሞት መቀነስ፣ በዓለም የታዳሽ ኃይል አቅም መስፋፋትም ከሚጠቀሱ ለውጦች መካከል መሆናቸውን አመላክቷል፡፡
ጊዜው አስፈላጊ በመሆኑ እና ይህንን እድል መጠቀም ስለሚገባ÷ከፈረንጆቹ መስከረም 22 እስከ 23 ቀን 2024 በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት የሚካሄደው ጉባኤ ዓለምን ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመመለስ ወሳኝ ይሆናል ማለቱን ከድርጅቱ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።