የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በጅማ ከተማ በፓናል ውይይት ታስቦ ዋለ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አለም አቀፉ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በጅማ ከተማ በፓናል ውይይት ታስቦ ውሏል።
የኤችአይቪ ኤድስ ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ31ኛ ጊዜ እየተከበረ ሲሆን፥ “ማህበረሰቡ የለውጥ አካል ነው” በሚል መሪ ቃል ነው በኦሮሚያ ክልል ደረጃ እየተከበረ የሚገኘው።
በኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ነጋሽ ስሜ የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት በሀገር አቀፍ ደረጃ 0.9 በመቶ በኦሮሚያ ክልል 0.6 በመቶ መሁንና በኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት ጥናት መረጋገጡን ገልፀዋል።
ከዚህም ሌላ ባለፉት ዓመታት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበር የጠቆሙት ምክትል ሀላፊው የስርጭቱ መቀነስ መዘናጋትን መፍጠሩን ተናግሯል።
በመሆኑም የቫይረሱ ስርጭት ዳግም እንዳይቀሰቀስ የሀይማኖት አባቶች ትምህርት ቤቶች ሚዲያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ህዝቡን ሊያነቁ ይገባል ብለዋል።
በስነስርዓቱ ላይ ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖችና ከተሞች የተውጣጡ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል።
በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልልም “ኤች አይቪ/ኤድስን በመግታት ረገድ የወጣቶችና አፍላ ወጣቶችን ሚና እናጎልብት” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በፓናል ውይይቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት በሽታው የነገ ሀገር ተረካቢ በሆነው አፍላ ወጣት ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመሆኑም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት በሁሉም ወረዳዎች የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት በወረዳ ደረጃ መቋቋሙ ስርጭቱን ለመግታት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽ ስራዎች የቫይረሱ ስርጭት ከ6 ነጥብ 5 ወደ 4 ነጥብ 8 ማውረድ የተቻለ ቢሆንም አሁንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተቀመጠው 0 ነጥብ 9 አንፃር ሲታይ ብዙ መስራትን እንደሚጠይቅ የክልሉ የፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በሙክታር ጠሀ