Fana: At a Speed of Life!

የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ለአገልግሎት ዘርፍ ኢንቨስትመንት መጎልበት ሚናው የጎላ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ከስራ ፈጠራ ባሻገር ለአገልግሎት ዘርፍ ኢንቨስትመንት መጎልበት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ኢኒሼቲቭን በዛሬው ዕለት በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን÷ በተጓዳኝ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር)÷ ኢኒሼቲቩ የትምህርት ዘርፉ ብቁ ትውልድ ለመገንባት በሚያከናውነው ስራ ላይ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

በተለይ ትውልዱ በንድፈ ሃሳብ የሚያገኛቸውን እውቀቶች በቀላሉ ወደ ተግባር እንዲለውጥ ምቹ እድል በመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ÷ቴክኖሎጂ ከስራ ፈጠራ ጋር የሚተሳሰር ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስትን ወክለው በፓናሉ የተሳተፉት አብዱልአዚዝ አልጃዝሪ÷ በኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂን እውን በማደረግ ረገድ ከፍተኛ የሆነ የአመራር ቁርጠኝነት መኖሩን አንደታዘቡ ተናግረዋል፡፡

ይህ ደግሞ በኢኒሼቲቩ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት አቅድ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ያብራሩት ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በእቅዱ ላይ ዲጂታል ክህሎትን መሰረት ያደረገ የሰው ኃይል ልማት ትኩረት እንደተሰጠው ጠቅሰው፤ ኢኒሼቲቩም ይህን እውን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢኒሼቲቩ በኢትዮጵያ ክህሎት ያለው የሰው ሃይልን በመገንባት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በአገልግሎቱ ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር)÷ ዘመናዊና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን እውን ማድረግ መንግስት እያከናወነ ያለው የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.