መከላከያ ብቁ የጦር አመራር ለመፍጠር ከምንጊዜውም በላይ እየሰራ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መከላከያ ብቁ የሆነ የጦር አመራር ለመፍጠር ከምንጊዜውም በላይ በመስራት ላይ ይገኛል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመከላከያ ዋር ኮሌጅ ለመደበኛና ለአጭር ኮርስ ተማሪ የ2016 ዓ.ም ተመራቂዎች የመመሪያ ንግግር አድርገዋል።
ተመራቂዎች ወደ ምድብ ቦታቸው ሲገቡ በትምህርት የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር በዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ የራሳቸው ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለባቸዉም ነው የገለጹት።
መከላከያ በስትራቴጂክ አመራርነት የበቃ መሪ ለማፍራት በተቋም ደረጃ ዕቅድ ነድፎ የአሰራር ስርዓትን ዘርግቶ ወጥ በሆነ መልኩ የላቀ የጦር አመራር ለመፍጠር ከምንጊዜውም በላይ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በዘመናዊ ሠራዊት ስርዓተ-ግንባታ በእውቀትና በክህሎት የሚመራ መሪና ተመሪ መፍጠር የሚቻለው እንደመከላከያ ዋር ኮሌጅ ያሉትን ተቋማት በማጠናከርና የአሰራር ስርዓታቸውን በማዘመን ጠንካራ ሠራዊት መገንባትና ከወገንተኝነት የፀዳ የአስተሳሰብ ልዕልና ያለው አመራር መፍጠር ተችሏልም ነው ያሉት፡፡
ሀገርን መታደግ የሚቻለው ከቅጥረኛ አስተሳሰብ የፀዳ አስተሳሰብ ያለው ሠራዊት መፍጠር ሲቻልና የተማረ ብቁ አመራር እና ተመሪ ሲኖር እንደሆነ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ትምህርት ላይ የነበራችሁ አመራሮች ወደ ስራ ስትገቡ በላቀ የአመራር ብቃትና በለውጥ አራማጅነት ግንባር ቀደም በመሆን ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደምታሸጋግሩ ሙሉ እምነት አለኝ ሲሉም ገልፀዋል፡፡