ለመቻል ስፖርት ክለብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ”መቻል ለኢትዮጵያ” ንቅናቄ ለመቻል ስፖርት ክለብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡
ለንቅናቄው ከታቀደው መርሐ ግብር 99 በመቶው የሚሆነውን ማሳካት እንደተቻለም ተጠቁሟል።
የመቻል ስፖርት ክለብ ቦርድ ሰብሳቢ ሰይፈ ጌታሁን (ዶ/ር) ÷የመቻል ለኢትዮጵያ ንቅናቄ በታቀደለት መርሐ-ግብር መካሄዱን አውስተው ለመርሐ-ግብሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብሩም ወደ 1 ቢሊየን ብር ገደማ ገንዘብ መሰብሰቡን ነው የገለጹት፡፡
የስፖርት ክለቡ 80ኛ ዓመት ክብረ በአል አካል የሆነው “መቻል ለኢትዮጵያ” የሩጫ ውድድር በየዓመቱ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
ክለቡ የራሱ መለማመጃ ስታዲየም እና አካዳሚ እንዲኖረው ማድረግ የንቅናቄው ዋነኛ አላማ በመሆኑና ያንን ለማሳካት እንደሚሰራ መናገራቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡
የመቻል ስፖርት ክለብ ዳይሬክተር ኮሎኔል ደረጀ መንግስቱ በበኩላቸው÷ የ”መቻል ለኢትዮጵያ” ንቅናቄ እንዲሳካ በማድረጉ ሒደት የሚድያዎች ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡