Fana: At a Speed of Life!

ኅብረቱ እና ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት የዓረብ ባንክ ለአኅጉሪቱ ዕድገት በጋራ እንደሚሠሩ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ኅብረት እና ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት የዓረብ ባንክ ለአኅጉሪቱ ዕድገት በአጋርነት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የግማሽ ዓመት ግምገማ ጉባዔ በጋና አክራ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ከጉባዔው ጎን ለጎንም የአፍሪካ ኅብረት እና ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት የዓረብ ባንክ አፍሪካን ለማልማት ብሎም ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል የዓረብ-አፍሪካ ፋይናንሺያል ጥምረት በይፋ ተመስርቷል፡፡

በዚሁ ወቅትም የጋና ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ በአፍሪካ እና በዓረብ ሀገራት መካከል ያለው ጠንካራ አጋርነት ልማትን በቅንጅት ለማስፋፋት ትክክለኛ ርምጃ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት እና ከጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች እስከ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ድረስ ውስብስብ እና ዘርፈ-ብዙ ፈተናዎች ከፊታችን ተደቅነዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ተግዳሮቶች ለማሸነፍም እንደዚህ ዓይነት ጠንካራ አጋርነቶች ያስፈልጉናል ማለታቸውን ዥንዋ ዘግቧል፡፡

ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት የዓረብ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ፋሃድ አልዶሳሪ በበኩላቸው፥ የአፍሪካን ፈጣን ልማት በቀጣዮቹ 50 ዓመታት ለማሳካት ጥምረቱ በተጣለበት ጊዜ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.