የአፍሪካ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲፋጠን ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲፋጠንና የአህጉሪቱ ዜጎችን ፍላጎት እንዲሳካ ተጠይቋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ከቡድን 20 እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጋር ከመገናኘቱ በፊት በአፍሪካ ውህደት ላይ ለመወያየትና አንድ ወጥ አቋም ለመያዝ በጋና ምክክር ተደርጓል።
በምክክሩም የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሆኑት የሞሪታኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት መሃመድ ኡልድ ጋዙዋኒ አህጉራዊው የኢኮኖሚ ውህደት ሂደት እንዲፋጠን አሳስበዋል፡፡
ይህም አህጉሪቱን ለመደገፍ እና የዜጎችን ፍላጎት ለማሳካት ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ማፋጠን አስፈላጊ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
የውህደቱን ሂደት ለመደገፍም ለአፍሪካ ህብረት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ አቅርቦት ላይ ምክክር መደረጉንም የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው፥ የህብረቱ አባል ሀገራት በቀጣይ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት አህጉር አቀፋዊ የጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት አባል በሆነበት የቡድን 20ን ጨምሮ በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች በአንድ ድምፅ መናገር አስፈላጊ መሆኑንም ነው ያሰመሩበት፡፡