Fana: At a Speed of Life!

የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችል መርሐ ግብሮችን ነድፍያለሁ – ኮርፖሬሽኑ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል መርሐ ግብሮችን መንደፉን የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

መርሐ ግብሮቹን ተግባራዊ ለማድረግ የፋይናንስ አቅሙን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀምና በ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ባደረገው ውይይት ላይ አስታውቋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኮርፖሬሽኑ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱንና የኮሪደር ልማት አካል በሆኑ የኮርፖሬሽኑ ሕንጻዎችና ይዞታዎች ላይ የዕድሳትና የማስዋብ ሥራ መስራቱ ተመላክቷል፡፡

ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሕንጻዎች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉንና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ግንባታዎች ደግሞ የማጠናቀቂያ ስራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከ86 በላይ ህንፃዎችን በማደስ የከተማዋን መስፈርት እንዲያሟሉና ውብ ገጽታ እንዲላበሱ ማድረግ መቻሉም ተነስቷል፡፡

የግንባታ ግብዓት እጥረትን ማቃለል የሚያስችሉ ብሎም እንደሀገር ተጨማሪ አቅም መሆን የሚችል የአርማታ ውህድና ብሎኬት ማምረቻ ማዕከልን ተከላውን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉም ተገልጿል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.