የአገልግሎት መስጫዎቻችንና የአሰራር ስርዓታችንን ለማሻሻል በትኩረት እንሰራለን – ከንቲባ አዳነች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአገልግሎት መስጫዎቻችንና የአሰራር ስርዓታችን ላይ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ስራዎች ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደገለጹት ፥ የ2016 በጀት ዓመት የገቢ አሰባሰብ ስራችንን በስኬት አጠናቅቀን በ2017 ለመሰብሰብ የተያዘውን ገቢ በጋራ ለማሳካት የሚያስችል የንቅናቄ መርሐ-ግብር ዛሬ ጠዋት አካሂደናል።
በመርሐ-ግብሩም በ2016 በገቢ አሰባሰብ የተሳተፉ እና ለውጤታማነቱ አስተዋፅዖ ያበረከቱ አካላትን ሁሉ አመስግነው ፥ በ2017 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደውን የ230 ቢሊየን ብር ገቢ እንዲሳካም አደራ ብለዋል፡፡
በ2016 ተሰበሰበውን 146 ቢሊየን ብር ከብክነት ተጠብቆ የህዝቡን የኑሮ ጫና የሚያቃልሉና የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ በጠቅላላ 18 ሺህ 91 ፕሮጀክቶችን ተሰርተው የተሰበሰበውን ገቢ መልሰው ለከተማዋ ልማት በማዋል ግብር ከፋዮችን በታማኝነት የሰጡትን ገንዘብ በሚገባው ስራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል ከንቲባዋ፡፡
አክለውም ፥ ለገቢ ቤተሰቦቻችን ሁሉ፤ ከተማችን የምታመነጨው የገቢ አቅም ከዚህ በላይ መሰብሰብ እንደምንችል የሚያሳይ በመሆኑ ከብክነት፣ ከብልሹ አሰራር እና ከሙስና በጸዳ መንገድ በ2017 ያቀድነውን 230 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ በጋራ እናሳካ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ዓመት ለተገልጋዮቻችን ክብር ስንል የአገልግሎት መስጫዎቻችን እና የአሰራር ስርዓታችን ላይ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ስራዎች ትኩረት ሰጥተን የምንሰራ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡