Fana: At a Speed of Life!

ማይክሮሶፍት የአይቲ መቆራረጥ ችግሩን ፈትቻለሁ ቢልም ኩባንያዎች አሁንም እየተቸገሩ እንደሆነ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ማይክሮሶፍት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ላይ ያጋጠመውን እክል ፈትቻለሁ ቢልም የተለያዩ ኩባንያዎች ግን አሁንም እየተቸገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የችግሩ ምንጭ እንደሆነ የተነገረለት ክራውድስትራይክ የተሰኘው የሳይበር ደህንነት ኩባንያ ኃላፊ ጆርጅ ኩርትዝ ሁሉም ስርዓቶች ወደነበሩበት እና ወደ ስራ ከመመለሳቸው በፊት ትንሽ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ገልጸው፤ ለተፈጠረው እክል ይቅርታ ጠይቀዋል።

የሶፍትዌር ችግሩ ቢቀረፍም እያንዳንዱ ጉዳት የደረሰበትን የማይክሮሶፍት ኮምፒውተር ዳግም ማስነሳቱ ትልቅ ስራ እንደሚፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በሺዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ተሰርዘዋል፣ የባንክ፣ የህክምና ማዕከላት እና የክፍያ ሥርዓቶች ሁሉም ተጎድተዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የጤና ተቋማት የታማሚዎቻቸውን የህክምና ታሪክ የሚያሳይ ዳታ ማግኘት ባለመቻላቸው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ተቸግረዋል።

በርካታ የአየር ማረፊያዎች በረራ ለመሰረዝ ወይም ለማዘግየት ተገደዋል።

ባንኮችም በተመሳሳይ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ክፍያዎችን ማስተናገድ አልቻሉም።

መገናኛ ብዙሃን የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍን ጨምሮ በተለያዩ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ እክል እንደገጠማቸው የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።

በርካታ አየር መንገዶች ያጋጠማቸው የአይቲ ችግር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያልገጠመው መሆኑን አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.