የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተመድ ጋር በጋራ በሚሰሯቸው ጉዳዮች ላይ መከረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ከተባበሩት መንግስታት ተቋማት ጋር በትብብር መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እና የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድ የተባበሩት መንግስታት ረዳት ሴክሬተሪ ጀነራል እና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አልካባሮቭ(ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የስነህዝብ ፈንድ ፕሮግራም ተወካይ ታይዎ ኦሉዮሚን ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ጊዜም የስራ ኃላፊዎቹ በዋናነት ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን መከላከል እና የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮ ለመስራት በሰፊው ተወያይተዋል።
በተጨማሪም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተለይም ደግሞ ያለዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል እንዲሁም ሴት ወጣቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የሚያግዙ ስራዎችን በጋራ መስራት ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል።
በተነሱ አጀንዳዎች ዙሪያ በቀጣይ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት በጋራ ለመምከርና መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ውይይት እንደሚካሄድ መገለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡