አየር መንገዱ የጉዞ ትኬታቸውን በኢትዮጵያ የሚገዙ የውጭ ዜጎች በውጭ ምንዛሬ መክፈል እንዳለባቸው አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጉዞ ትኬታቸውን በኢትዮጵያ የሚገዙ የውጭ ሀገር ዜጎች በውጭ ምንዛሬ መክፈል እንዳለባቸው አስታውቋል፡፡
አየር መንገዱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው ማብራሪያ÷ ለመንገደኞች የሚሰጠውን ዓለም አቀፍ የበረራ ቲኬት ሽያጭ አገልግሎቶች በሙሉ በውጪ ምንዛሪ ብቻ እንደሚሆን ተደርጎ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ሲዘዋወር መመልከቱን አንስቷል፡፡
ይሁን እንጂ የጉዳዩ ትክክለኛ መረጃ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም መመርያ ማውጣቱን ተከትሎ አየር መንገዱ ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ ለሚደረጉ ጉዞዎች በሀገር ውስጥ መገበያያ ገንዘብ ሲሰጥ የነበረውን የቲኬት ሽያጭ አሰራር ከሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በከፊል የተከለከለ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ስለሆነም እነዚህ መንገደኞች በውጪ ምንዛሬ አገልግሎቱን የሚያገኙ መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡
ይህም ሀገር ውስጥ በሚንቀሳቀሱ በሁሉም አየር መንገዶች ተግባራዊ እንዲደረግ የወረደ መመሪያ መሆኑን አሳስቧል፡፡
ኢትዮጵያዊያን እና ህጋዊ ሰነድ ያላቸው ማለትም የመኖሪያ ፈቃድ፣ ቢጫ ካርድ፣ የሥራ ፈቃድ፣ የዲፕሎማቲክ ፈቃድ ወዘተ ያላቸው የውጪ ሀገር ዜጎች በሙሉ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጪ ሀገራት ለሚደረጉ በረራዎች የቲኬት ሽያጭ አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር መሰረት ማግኘት የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ነገር ግን ትኬታቸውን በኢትዮጵያ የሚገዙ የውጭ ሀገር ዜጎች በውጭ ምንዛሬ መክፈል ይኖርባቸዋል ነው ያለው አየር መንገዱ።