Fana: At a Speed of Life!

ከስርዓተ-ምግብና ጤና ጋር የተያያዙ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሊሆኑ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ጋር በመተባበር ከስርአተ-ምግብ እና ጤና ጋር የተያያዙ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሚሆኑ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የዩኤስኤይድ ኒውትሪሽን ቡድን አባላት ስርአተ-ምግብ፣ ልማትና ሰላምን አጣምሮ በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘውን ትሪፕል ኔክሰስ ፕሮጀክት በሚደገፍበት ሁኔታ ላይ ከጤና ሚኒስቴር ኒውትሪሽን ዴስክ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ÷ ዩኤስኤይድ አዳዲስ ከስርአተ-ምግብ ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶችን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መተግበር እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ለሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ትብበር እንደሚያደርግም ዶክተር መቅደስ አረጋግጠዋል፡፡

ፊድ ዘ ፊዩቸር በዩኤስኤይድ የሚተገበር የስርአተ-ምግብ ፕሮግራም ሲሆን÷ ሴቶች፣ ታዳጊ እና ጨቅላ ህጻናት የተሻለ ስርአተ-ምግብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡

ስርዓተ-ምግብ ዩኤስኤይድ በኢትዮጵያ ከሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን የተናገሩት የድርጅቱ ስርአተ-ምግብ ቡድን መሪ ፓትሪክ ዌብ÷ በኢትዮጵያ እየተተገበሩ የሚገኙ የስርአተ-ምግብ ፕሮጀክቶች ውጤት እያስገኙ መሆኑን እንደሚረዱ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ዩኤስኤይድ ለስርአተ-ምግብ ፕሮጀክቶች መተግበሪያ የሚሆን የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍን ለማስቀጠል ማሰቡን የድርጅቱ ግሎባል ሄልዝ ኑትሪሽን ዲቪዥን ሃላፊ ኬሊ ስቱዋርት ተናግረዋል፡፡

ዩኤስኤይድ በሀገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ ቀጣይነት ያለው የምግብ ምርት በማምረት የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመከላከል እንዲቻል ድጋፍ እንደሚያደርግም መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.