ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በራሳቸውን ገንዘብ ለመገበያየት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለግብይት የራሳቸውን ገንዘብ ለመጠቀም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ ፥ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዢ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ ፈርመዋል፡፡
በዚህም በሁለቱ ሀገራት ለሚደረግ ግብይት የራሳቸውን ገንዘብ ማለትም ድርሃምና ብር ለመጠቀም ነው ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡
ሁለቱ አካላት ለተግባራዊነቱ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ጥረት እንደሚያደርጉም ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የኢትዮጵያ አንዷ የንግድ አጋርና የውጪ ኢንቨስትመንት ምንጭ ናት፡፡
በዚህም ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናክርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረት ቀጣይነት ያለው ልማትና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዥ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ በበኩላቸው ፥ ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ መምጣታቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡