ናይጄሪያዊው ቱጃር አሊኮ ዳንጎቴ ከሀገሬ ውጭ ቤት የለኝም አሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ናይጄሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ ከሀገሬ ውጪ ቤት የለኝም ሲሉ በመግለጽ ብዙሃኑን የሀገራቸውን ዜጎች አስገርመዋል።
ዳንጎቴ በትውልድ ከተማቸው ካኖ እንዲሁም በሌጎስ ካሏቸው ሁለት ቤቶች በስተቀር የመኖሪያ ቤት እንደሌላቸው ገልጸው፤ ወደ ሀገሪቱ ዋና ከተማ አቡጃ ለጉብኝት ሲሄዱ በተከራዩት አፓርታማ ውስጥ እንደሚያርፉ ተናግረዋል።
በጥር ወር በፎርብስ መፅሔት በአፍሪካ ለ13 ተከታታይ ዓመታት በአፍሪካ ከፍተኛ ባለጸጋ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ቱጃሩ ዳንጎቴ፤ ሀብታቸው ባለፈው ዓመት በ400 ሚሊየን ዶላር ከፍ ያለ ሲሆን÷ በዚህም የተጣራ 13 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር እንዳላቸው በወቅቱ ገልጿል።
የ66 ዓመቱ ነጋዴ በሲሚንቶ እና በስኳር ዘርፍ ተሰማርተው ሀብት ያፈሩ ሲሆን÷ ባለፈው ዓመት በናይጄሪያ የኢኮኖሚ ማዕከል በሆነችው ሌጎስ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ መክፈታቸውን የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።
ባሳለፍነው እሁድ በዳንጎቴ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከፍተኛ ሀብት ያላቸው ቢሆንም ከሀገራቸው ናይጄሪያ ውጭ የመኖሪያ ቤት እንደሌላቸው ገልጸዋል።
ይህ ገለጻቸው ብዙ ናይጄሪያውያን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በበጎነቱ እየገለጹትና እየተቀባበሉት እንደሚገኙ ዘገባው አመላክቷል፡፡
ብዙዎቹ የናይጄሪያ ባለሃብቶች በለንደን፣ ዱባይ እና አትላንታ ቤቶች እንዳላቸው ይነገራል።
ዳንጎቴ ከሀገራቸው ውጭ “በለንደን ወይም በአሜሪካ ቤት የለኝም ምክንያቱ ደግሞ የናይጄሪያን ኢንዱስትሪ ማሳደግ ላይ ማተኮር ስለፈለኩ ብቻ ነው” በማለት ገልጸዋል።
ዳንጎቴ በፈረንጆቹ 1996 በለንደን የሚገኘውን ቤታቸውን እንደሸጡ የተናገሩ ሲሆን÷ ከሽያጩ የተገኘውን ገንዘብም ወደ ንግዳቸው እንዳስገቡት ተናግረዋል፡፡