አካል ጉዳተኝነት ከምፈልገው መዳረሻ የሚያግደኝ ሳይሆን ይበልጥ የሚያተጋኝ ሆኗል – ተማሪ ኬይራ ጀማል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፈጥሮ ሁለት እጆች የሌላትተማሪ ኬይራ ጀማል እግሮቿን እንደ እጇቿ ተጠቅማ የተለያዩ ተግባራትን ትከውናለች።
ዛሬ መሰጠት በጀመረው የተፈጥሮ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናም እግሯን በመጠቀም በመፈተን ላይ ነች።
አካል ጉዳተኝነት ከምፈልገው መዳረሻ የሚያግደኝ ሳይሆን ይበልጥ የሚያተጋኝ ሆኗል የምትለው ተማሪዋ፤ የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ ስትሆን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፈተናውን እየወሰደች ትገኛለች።
መምህራንና የዩኒቨርሲቲው አመራር በተማሪዋ ብቃት እና ችሎታ ብቻ ሳይሆን ባላት የስነ ልቦና ጥንካሬ እና መተማመን ይደሙማባታል።
የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን በማሪያም ሰፈር 1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት ያጠናቀቀች ሲሆን በቆይታዋ ታታሪና የደረጃ ተማሪ መሆኗን መምህራኖቿ ይመሰክራሉ።
ዛሬ በተጀመረው የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ከእኩዮቿ ጋር በመውሰድ ላይ ስትሆን፤ ፈተናውን በአንድ ድጋፍ ሰጪ መምህር በመታገዝ እግሮቿን እንደ እጆቿ በመጠቀም በበይነ መረብ የሚሰጠውን ፈተና እየወሰደች ነው።
ፈተናውን በበቂና በተሻለ ውጤት በማለፍ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደምትገባም በሙሉ ልብ ተናግራለች ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
ዛሬ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውን የተፈጥሮ ሳይንስ ሀገር አቀፍ ፈተና ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ተማሪዋ በልዩ ክፍል ስትፈተን አግኝተው አበረታተዋታል።
ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ምሳሌ ናት፤ ያላትን ጥንካሬ አድንቄያለሁ፤ የምትፈልገው ደረጃ እንደምትደርስ ተስፋ አለኝ ብለዋል።
ተማሪ ኬይራ ጀማል አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆኑን በተግባር እያሳየች መሆኑ ተገልጿል።