ክሱ የቀረበው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የህገመንግስትና በህገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከተው ችሎት ነው።
ክሱ የቀረበባቸው ተከሳሾች 1ኛ/ መርጋ ሙሉነህ በንቲ (ጃል ሎላ)፣ ገለታ በቀለ ቡልቻ፣ መገርሳ ሶማ ዶጃ፣ ዋቅጅራ ጌታቸው መርዳሳ፣ ዋዳ ጌታቸው ጊንዳሳ እና ሳሙኤል ኢስራኤል ቶማስ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።
ተከሳሾቹን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከድሬዳዋ ፖሊስ አባላትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ የምርመራ ማጣሪያ በማከናወን ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በስድስት ግለሰቦች ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ተደራራቢ የሽብር ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በ1ኛ ተከሳሽ መርጋ ሙሉነህ በንቲ (ጃል ሎላ) ላይ በቀረበው ክስ÷ ግለሰቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የሸኔ ቡድን አባል በመሆን ከጳጉሜ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አባይ ጮመን ወረዳ ባቱ በሚባል አካባቢ ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ በኦሮሚያ ክልል በሆሮጉድሩ ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በጂማ እና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች ከሌሎች ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን ለሽብር ወንጀል ተግባር ሲንቀሳቀስ እንደነበር ተመላክቷል።
በተለይም በመስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም ተከሳሹ ከሌሎች ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ወደ ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ በመንቀሳቀስ የፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ በመክፈት ጉዳት ማድረሱ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም የወረዳውን አስተዳደር ጽ/ቤት ንብረት እና የሌላ የፀጥ አካላት ተሽከርካሪዎችን፣ ሞተር ሳይክሎችን በማቃጠል፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሊቦ ቅርጫፍ እና ከአዋሽ ባንክ ካዝና በመስበር 10 ሚሊየን 658 ሺህ 783 ብር መዝረፋቸው በክሱ ተመላክቷል።
ሌሎችም ተከሳሾች በተለይ ምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ አካባቢ ለሚንቀሳቀሱ የሸኔ የሽብር ቡድን አባላት የጦር መሳሪያ፣ የተለያዩ የሎጂስቲክ ድጋፎችን በማድረግ ተሳትፎ እንዳላቸው በክስ ዝርዝሩ ላይ ዐቃቤ ሕግ ጠቅሷል።
5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ደግሞ በመጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም በ1ኛ ተከሳሽ ስም ከአዲስ አበባ አራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 2 ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ ማዘጋጀታቸው በክሱ ተመላክቷል።
በዚህ መልኩ ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው በዐቃቤ ሕግ የተመሰረተባቸው ዝርዝር ክስ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ተከሳሾቹ ከቤተሰብ ጋር አለመገናኘታቸውን ጠቅሰው፤ ከጠበቃ ጋር ተገናኝተው ተማክረው ለመቅረብ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ፍርድ ቤቱ ከጠበቃ ጋር ተማክረው እንዲቀርቡ ለመጪው ዓርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ