በሞጆ ከተማ በ75 ሚሊየን ብር ለሚገነባው 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘የአሽከርካሪዎች ድምጽ በጎ አድራጎት’ የተሰኘ ማህበር በ75 ሚሊየን ብር በሞጆ ከተማ ለሚያስገነባው የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ት/ቤቱ በተቀመጠለት ጊዜ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ሚኒስቴሩ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡
ሌሎች የዘርፉ ማህበራትም የአሽከርካሪዎች ድምጽ በጎ አድራጎት ማህበርን ፈለግ እንዲከተሉ ነው የጠየቁት።
አሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ ማህበራት የጭነትና የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በማህበራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሞጆ ከተማ ከንቲባ ገዛሊ ሀሹ በበኩላቸው÷ የከተማ መስተዳድሩ በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና የትምህርት ተቋማት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ባሉት ላይ በተሰራው ሥራ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።