የቶንሲል ምልክቶችና መከላከያ መንገዶች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጉሮሮአችን ውስጥ በግራና በቀኝ በኩል ሁለት የቶንሲል ዕጢዎች የሚገኙ ሲሆን÷ የእነዚህ ዕጢዎች በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ መጠቃት ቶንሲል የተሰኘ በሽታ ያመጣል፡፡
በጣም የሚታወቀው ቶንሲልን የሚያስከትለው ባክቴሪያ ደግሞ “ስትሬፕቶኮከስ ፓዮጂንስ” ይባላል፡፡
የቶንሲል ህመም ምልክቶች:-
የሁለቱ የቶንሲል ዕጢዎች ቀልተው ማበጥና ቢጫ ወይም ነጣ ያለ ምልክት መታየት፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ምግብ ለመዋጥ መቸገር፣ አንገት ስር ያሉ “ሊምፍኖድስ” የተባሉ ዕጢዎች ማበጥ ወይም መጠኑ መጨመር፣ ከፍተኛ ድካም (ለሕፃናት)፣ መጥፎ አተነፋፈስ፣ የምላስ መድረቅና የድምፅ መታፈን ናቸው፡፡
እንዲሁም የአንገት መገተር፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የሆድ ሕመም (በወጣት ልጆች ላይ)፣ ጀርባን፣ እጅንና እግርን ማሳከክ በቶንሲል ስለመያዛችን የሚጠቁሙ ምልክቶች መሆናቸውን ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የቶንሲል በሽታን እንዴት እንከላከል?
ልጆች ከመፀዳጃ ቤት መልስ እና ምግብ ከመመገብ በፊት ሁል ጊዜ እጅን በውሃና በሳሙና በአግባቡ እንዲታጠቡ ማድረግ፤ መጠጫ ብርጭቆዎች፣ የፕላስቲክ ጠርሙሶችና ሌሎች የመመገቢያ ዕቃዎችን ከሌሎች ልጆች ጋር እንዳይጋሩ ማድረግ፡፡
በተጨማሪ ልጆች ቶንሲል ሕመም እንደያዛቸው ከተረጋገጠ የጥርስ ብሩሽን መቀየር፣ ከታመሙ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ማድረግ፣ በሚስሉበትና በሚያስነጥሱበት ጊዜ በሶፍት ወይም በክንድ እንዲሸፍኑ ማድረግና ካሳላቸውና ካስነጠሳቸው በኋላ እጃቸውን በውሃና በሳሙና እንዲታጠቡ ማስተማር የቶንሲል ህመምን ለመከላከል ይረዳል።