ከግሎባል ፈንድ በተገኘ ድጋፍ ስኬታማ በሽታዎችን የመከላከል እና የመቆጣጠር ተግባራት ተከናውኗል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከግሎባል ፈንድ በተገኘ 453 ሚልየን ዶላር የቲቢ፣ የኤች አይ ቪ፣ የወባ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም የጤና ስርአትን በማጠናከር ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በበሽታ መከላከል ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን ለማስፋፋትና ያጋጠሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ዐውደ ጥናት ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የኢትዮጵያ መንግስት የጤናውን ስርዓት ለማጠናከር በሚያከናውናቸው ተግባራት ግሎባል ፈንድ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኤች አይ ቪ፣ የወባ እና የቲቢ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚተገበሩ ስራዎች ላይ ለሚያከናውናቸው የድጋፍ ተግባራት እና ላበረከተው አስተዋጽኦም አመስግነዋል፡፡
ከግሎባል ፈንድ በተገኙ ድጋፎች የኤች አይ ቪ፣ የወባ እና የቲቢ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
በቀጣይ የተገኙ ውጤቶችን ለማስፋፋትና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ስራዎችን መተግበር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ የ440 ሚልየን ዶላር ፕሮጀክቶች ትግበራን በፍጥነት ለመጀመር ከክልሎች፣ ኤጀንሲዎች እና አጋር ድርጅቶች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱም ተገልጿል፡፡