እንቅስቃሴያችን የእርስ በርስ ትስስርና አንድነትን የሚያፀና ተግባር ነው – በጎ ፈቃደኞች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የበጎ ፍቃድ ስራ ላይ መሳተፋቸው የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነትን በማፅናት የበጎ ፍቃድ ስራ እንዲያብብ እያገዘ መሆኑን ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ ስራ ተሳታፊ ወጣቶች ተናገሩ።
ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የወሰን ተሻጋሪ ወጣት የበጎ ፍቃደኞች ዛሬ በድሬዳዋ ችግኞች በመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አካል ሆነዋል።
ወጣቶቹ በድሬዳዋ ቆይታቸው ከችግኝ መትከል ባሻገር ለአሸዋ የገበያ ማዕከል የእሳት አደጋ ተጎጂዎችም ድጋፍ አድርገዋል ነው የተባለው።
በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉት ወጣቶች እንደተናገሩት ፥ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ ስራ ተሳታፊ ወጣቶች ባላቸው ዕውቀትና ጉልበት ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል እየተጉ ናቸው።
የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ እንደተናገሩት፥ “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ ከመላው ሀገሪቷ የተሰባሰቡ ወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች ድሬዳዋ ተገኝተው በበጎ ተግባራት በመሰማራታቸው አስተዳደሩ ኩራትና ክብር ይሰማዋል።
ወጣቶቹ የእርስ በርስ ትስስርና አንድነትን አፅንተው ፤በራስ አቅምና ጉልበት ከተረጂነት ለመውጣት እንደሚቻል መንገድ ማሳየታቸውንም ገልፀዋል።
ወጣቶቹ “ለእኛም አርዓያ ሆነዋል፤ በክረምቱ ለጀመርናቸው የበጎ ስራዎች ትልቅ መነቃቃት ፈጥረዋል” ሲሉም አክለዋል።
ወጣቶቹ ወሰን ሳይገድባቸው በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውረው ደም በመለገስ፣ችግኞች በመትከል፣ በግንዛቤ ትምህርት፣ በአካባቢው ፅዳትና ውበት ላይ በመሳተፍ አርአያነታቸው እያሳዩ ናቸው ያሉት ደግሞ በኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እንደገና ፍቃዱ ናቸው።
ወጣቶች በቀጣዮቹ ቀናት በሐረር እና በጅግጅጋ ከተሞች ተገኝተው ተመሣሣይ ስራዎች እንደሚያከናውኑ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡