በበተያዘው መኸር ወደ 600 ሺህ ሄክታር መሬት በቦለቄ ዘር ሸፍነናል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በበተያዘው መኸር ወደ 600 ሺህ ሄክታር መሬት በቦለቄ ዘር ሸፍነናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የክልሉ መንግስት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የተመረጡ የሰብል ዝርያዎችን በተለያዩ የኢኒሼቲቭ ፓኬጆች በመደገፍ እና ልዩ ክትትል በማድረግ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
ከነዚህ መካከል የቅባት እህሎች ኢኒሼቲቭ፤ የቦሎቄ፣ የአኩሪ አተርና የሰሊጥ ሰብሎች የውጭ ምንዛሬ በማምጣትና የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሆነ አመልክተዋል።
በ2014/15 የምርት ዘመን 235 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቦለቄ በማልማት ከ3 ነጥብ 33 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት መቻሉን አስታውሰው፤ በዚህ ክረምት ወደ አንድ ሚሊየን ሄክታር በማልማት 14 ነጥብ 57 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በዚህም በእስካሁኑ አፈፃፀም ወደ 600 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ሸፍነናል ብለዋል።
በ2014/15 ምርት ዘመን 14 ሺህ 647 ሄክታር መሬት ላይ አኩሪ አተር በማልማት 290 ሺህ ኩንታል ምርት ተገኝቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህ አመት 600 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በማልማት ወደ 12 ሚሊዮን ኩንታል የአኩሪ አተር ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በእስካሁኑ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በ2014/15 የምርት ዘመን 49 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥ ለምቶ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ፤ በዚህ አመት ወደ ግማሽ ሚሊየን ሄክታር በማልማት 400 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅደናል ብለዋል።
ከዘንድሮው እቅድ ውስጥ እስካሁን 300 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም ጠቁመዋል።