የመጀመሪያ ዙር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሰጥ የቆየው የመጀመሪያ ዙር የ2016 ትምህርት ዘመን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተጠናቀቀ።
ከሐምሌ 3 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተሰጠው የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተና መጠናቀቁ ተገልጿል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በበይነ መረብና በወረቀት በድብልቅ የተሰጠው ፈተና በስኬት መጠናቀቁ ተመላክቷል።
የተፈጥሮ ሳይንስ ቀመር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈታኞች ደግሞ ከሐምሌ 9 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ፈተናውን ይወስዳሉ።
የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከ700 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በወረቀትና በኦላይን እንደሚሰጥ መገለፁ ይታወቃል፡፡
በትግራይ ክልል ደግሞ በሁለት ዙር ፈተናው የሚሰጥ ሲሆን ከሐምሌ 2 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይሰጣል።
ይህም የሆነው በቀድሞው ሥርዓተ-ትምህርት የተማሩ በ2013 እና በ2014 የትምህርት ዘመን መፈተን የነበረባቸው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተና የሚወስዱ በመሆኑ ነው።