Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ የወባ በሽታ መከላከል ግብረ ሃይል ገለጸ፡፡

የክልሉ የወባ ስርጭት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ29 በመቶ መጨመሩና በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ 53 ሺህ ሰዎች ላይ በሽታው መገኘቱ ተነግሯል።

በሽታው በ34 ወረዳዎች በከፍተኛ ሁኔታ የስርጭት አድማሱን በማስፋት 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሰዎች ለህመም መዳረጋቸው ተገልጿል።

ክልላዊ የወባ በሽታ መከላከል ግብረ ሃይል ሰብሳቢ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)÷ አሁን ያለውን የወባ ስርጭት ለመቆጣጠር በየደረጃው ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የመከላከል እቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዋነኛ የወባ መራቢያ ወቅት የሆነው መስከረም ከመምጣቱ በፊት ወረርሽኙን በመግታት የወባ በሽታን ለመከላከል ትኩረት እንደተሰጠ ተናግረዋል።

የመረጃ ሥርዓቱን በማሳለጥ የወባ በሽታ መረጃዎችን በየእለቱ በፍጥነት መሰብሰብ እየተሠራ ሲሆን ስርጭቱ ከፍተኛ በሆነባቸው 21 ወረዳዎችም የፀረ ወባ ኬሚካል የቤት ለቤት ርጭት በመካሄድ ላይ ይገኛልም ብለዋል።

የበሽታው ስርጭት እንዳይስፋፋም የግንዛቤ ማስፋት ሥራውም ጎን ለጎን ሊሠራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.