የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት 14 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓመት 14 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታውቀ።
በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እንዳመለከቱት፤ አገልግሎቱ የገቢ አሰባሰብ አሰራርን በማስተካከል ይባክን የነበረውን ገንዘብ በትክክል በመሰብሰቡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ገቢው በሶስት እጥፍ አድጓል።
ከፓስፖርት አሰጣጥ እና አመልካቾቹንም በተገቢው መንገድ ከመቀበል አንጻር በተሰራው ስራ የደንበኞች አገልግሎት ስራ መቀላጠፉን ገልጸዋል።
ተቋሙ እያካሄደ ባለው የለውጥ ስራ ውስጥ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ውሳኔዎች እግድ ላይ የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ ግለሰቦችን ነጻ ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው።
ከ34 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎችንም ጊዜያዊ እና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መሰጠቱም ተጠቁሟል።
ህጋዊ መንገድ ሳይከተሉ የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ የውጭ ዜጎችንም ህጋዊ እንዲሆኑ እና ከሃገር እንዲወጡ መደረጉ ተገልጿል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በጸደቀው አዲስ አዋጅ የተመላከተው የዋጋ ተመን ከነሃሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን አገልግሎቱ በሰጠው መግለጫ አመላክቷል።
ሲያጋጥም የነበረውን የፓስፖርት መዘግየት ችግር ለመፍታት እሁድን ጨምሮ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተነግሯል።
በይስማው አደራው እና ሰሎሞን ይታየው