Fana: At a Speed of Life!

የሶስቱ አናብስት አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት ቡድናቸው በጥንቃቄ እንዲጫዎት አስጠነቀቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት እሁድ በሚከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ቡድናቸው በጥንቃቄ እንዲጨዋት አስጠንቅቀዋል፡፡

አስደናቂውን የሉዊስ ዴ ላ ፉዌንቴ ቡድን በእለተ ሰንበት የሚገጥሙት የ53 ዓመቱ አሰልጣኝ÷ ቡድናቸው ስፔንን በማሸነፍ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫን ወደእጃቸው ለማስገባት ብርቱ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የስፔን ብሔራዊ ቡድን ጥሩ እግር ኳስ የሚጫዎት ቢሆንም አብዛኞቹ ተጫዋቾቻቸው ወጣትና ልምድ ያላካበቱ ስለሆኑ እንደመልካም አጋጣሚ እንደሚጠቀሙበት ሳውዝጌት ተናግረዋል፡፡

በ16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ለፍፃሜ ቀርበው በጣሊያን ብሔራዊ ቡድን በመለያ ምት ዋንጫውን ማጣታቸው የእሁዱን ፍፃሜ በድል ለመወጣት የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸው ገልፀው÷ ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

“ተጫዋቾቼ በጥሩ መንፈስ ላይ ናቸው፤ በትላልቅ መድረኮች የተጫወቱ ኮከቦች አሉኝ፤ በጨዋታው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ” ብለዋል፡፡

ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ ‹‹ሶስቱ አናብስት›› እየተባለ የሚጠራውን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ማሰልጠን የጀመሩት ጋሬዝ ሳውዝጌት በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ አሳማኝ ብቃት ማሳየት ባይችሉም ሳይታሰቡ ለፍፃሜው ደርሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር በእሁዱ ጨዋታ ቢያሸንፉም ባያሸንፉም የ53 ዓመቱን አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝ ጌት ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ማራዘም እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡

የእንግሊዝ የእሁድ ተጋጣሚዋ ስፔን የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዳኒ ካርቫሀል ከአንድ ጨዋታ ቅጣት በኋላ ወደ ሜዳ የሚመለስ ሲሆን አማካዩ ፔድሪ ግን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡

‹‹ላ ሮሀ (ቀዮቹ)›› በሚል ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት ስፔኖች ከምድብ ማጣሪያ ጀምሮ ያሉትን ስድስት ጨዋታዎች ከአሳማኝ ብቃት ጋር በማሸነፍ በመድረኩ አዲስ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡

ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ ለአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ መድረስ የቻሉት ስፔኖች÷ ዋንጫውን በፈረንጆቹ 1964፣ 2008 እና 2012  አንስተዋል፡፡

ስፔን እና እንግሊዝ በታሪካቸው ለ27 ጊዜያት ያህል እርስበርስ የተገናኙ ሲሆን እንግሊዝ 14ቱን በማሸነፍ የተሻለ የበላይነት ሲኖራት ስፔን ደግሞ 10 ጊዜ አሸንፋለች፡፡ ቀሪዎቹ ሶስት ግንኙነታቸውን በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።

በእሁዱ ፍልሚያ ከስፔን በኩል የ16 ዓመቱ ታዳጊ ላሚን ያማል እንዲሁም ከእንግሊዝ ደግሞ የ20 ዓመቱ አማካይ ጁድ ቤሊንግሐም በጨዋታው ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.